ኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በማጽናት ዓድዋን ለትውልድ ማሻገር የወጣቱ ትልቅ አደራ ነው /አቶ በላይ ደጀን/
ኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በማጽናት ዓድዋን ለትውልድ ማሻገር የወጣቱ ትልቅ አደራ ነው /አቶ በላይ ደጀን/
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ለ129 ኛው የዓድዋ ድል በዓል ያስተላለፉት መልዕክት
ከሁሉ አስቀድሜ "አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ለሚገኘው ለ129ኛው የአድዋ ድል በዓል የከተማችን ወጣቶች እና ስፖርት ቤተሰቦች እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ፡፡
ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን ተጠራርተው ለአንድ ዓላማ ለአገር ፍቅርና ክብር የተዋደቁበት የድል በዓል ሲሆን የጥቁሮችን የባርነት ቀንበር የሰበረ ዘመናዊ መሳሪያን የታጠቀን ኃይል በጦርና በወኔ ማንበርከክ እንደሚቻል ያሳየ አኩሪ ታሪካችን ነው።
ዓድዋ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መስረት በመሆን የነጻነት ታጋዮችን ያነቃቃ፣ የኢትዮጵያ ትንታግ አይበገሬ ጀግኖችን ለነጻነት እና ለአገር ፍቅር ስሜት የከፈሉትን መስወዕትነት የምናይበት ሕያው ምስክር በመሆኑ አዲሱ ትውልድ ለመጪው ትውልድ ትላንትን ማክበር፣ዛሬን በመኖር ነገን በመስራት አገር ወዳድነቱን በማስመስከር የአባቶቹ ልጅ መሆኑን ማሳየት አለበት፡፡
ውድ የከተማችን ወጣቶች እና የስፓርት ቤተሰቦች በሕብረ ብሔራዊ የአገር ፍቅርና ጀግነነት የኢትዮጵያ ትንሳኤ ለማረጋገጥ ታሪካችንን በማክበር የራሳችንን ታሪክ ለመስራት የምናደርገውን እልህ አስጨራሽ ጉዞ በእውቀታችሁ በጉልበታችሁ እና በጊዜያችሁ እንድታግዙ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
129ኛውን የዓድዋ ድል ስናከብር በወንድማማችነት በእህትማማችነት መንፈስ እንዲሁም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ የልማት ስራዎች ላይ በአርበኝነት ስሜት በመሳተፍ ሊሆን ይገባል፡፡
ጀግኖች አባቶቻችና እናቶቻችን በአድዋ ጦርነት ከጠላት ጋር ተናንቀው መስዋእትነት በመክፈል ያስረከቡንን ነፃ አገር በአንድነትና በትብብር ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሸጋገር የተጣለብን ትልቅ ኃላፊነት በኢትዮጵያዊ አብሮነትን እና በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ሕልውናችንን እንድታትረጋግጡ አደራ እላለሁ፡፡
የመላው ኢትዮጵያውያን ተጋድሎን በደማቁ የጻፈው የአድዋ ድል ምስጢር አባቶቻችን በመካከላቸው የነበረውን ልዩነት ወደ ጎን በማድረግ በፍጹም ጀግንነት ያደረጉት ተጋድሎ መሆኑ ይታወቃል፡፡አዲሱ ትውልድም የአገራችንን ደህነንት ለመጠበቅ እና ልማቷን ለማረጋገጥ በአርበኝነት፣ በአገር ፍቅርን ስሜት እና በአንድነት በመቆም ከፋፋይ አስተሳሰቦችን በመቅረፍ ትብብርን እንድትጸኑ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የጋራ ቤታችን የሆነችው አዲስ አበባ ሰላሟ እና ደህንነቷ እንዲረጋገጥ በህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት በመዛመድ የአያቶቻችንን የአርበኝነት ዘመን በእኛም ትውልድ በመድገም የብልጽግና ጉዞዎችንን ለማረጋገጥ በአንድነት በመቆም የኢትዮጵያን የከፍታ ለማረጋገጥ በጋራ እንድንቆም የአደራ መልዕክቴን አስተላልፋለው
በመጨረሻም ወጣቶች እና የስፖርት ቤተሰቦች በእኩልነት እና በአንድነት የሚያጋጥሙንን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ለመመከት በአባቶቻችን የአገር ፍቅር ስሜት ለዘመናት የሚሻገር ታሪክ እንስራ እያልኩ በዓሉ የአብሮነት፣የጀግነነት እና የሰላም እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን
የካቲት 23 2017 ዓ/ም
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.