ሀገር ዓቀፍ የስርዓተ ፆታ ማካተት ማኑዋል
መቅድም
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የልማት ስራ እንቅስቃሴ ውጤቶች በሴቶችና በወንዶች መካከል በእኩል ደረጃ ተደራሽ እንዲሆኑ ቁርጠኛ አቋም ይዞ ተንቀሳቅሷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሴቶችና ወንዶች በተመሳሳይ ሁኔታ የተለያዩ እድሎች ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ፣ እውቅናና ደረጃ እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህ የስርዓተ-ጾታ ማካተቻ ጋይድላይን በተቋም፣ በፖሊሲ፣ በፕሮግራም እና በፕሮጀክት ደረጃዎች ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በመለየት መንግስት በዚህ ረገድ ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያረጋግጣል፡፡
የዚህ የሥርዓተ-ጾታ ማካተቻ ጋድላይን ዓላማ ለመንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ አጋሮች እንዲሁም ለሌሎች ለዘርፍ እና ለክልል የሥርዓተ-ጾታ ማካተቻ ማኑዋሎች እንደ ማጣቀሻነትና ብሔራዊ ማዕቀፍ ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ ይህ ጋይድላይን በአብዛኛው በሁሉም የሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴዎች ሴቶች ከወንዶች እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸውና በእኩል ደረጃም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችሉ ቴክኒካዊ አካሄዶችን ለማመላከት የሚያስችል ነው፡፡ ይህ ሰነድ የስርአተ ጾታ ማካተት መርሆዎችን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊገነዘቡት በሚችሉበት አግባብ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ ጋይድላይኑ ለሁሉም ጉዳዮች መፍትሄ ሰጪ ሰነድ እንደሆነ ተደርጎ መታሰብ የለበትም፡፡ ይልቁንም ባለድርሻ አካላት በሚያመቻቸው መልኩ ሊጠቀሙበትና ሊያዳብሩት ይገባል፡፡ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ሁሉም ፈጻሚዎችና አጋሮች በልማት እንቅስቃሴዎቻቸው ውስጥ ይህንን ብሔራዊ የሥርዓተ-ጾታ ማካተቻ ጋይድላይን እንዲጠቀሙ ያበረታታል፡፡