ቢሮው የበጀት አመቱን 1ኛ ሩብ አመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን በመገምገም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከሰራተኞች ጋር ውይይት አካሄደ።
ቢሮው የበጀት አመቱን 1ኛ ሩብ አመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን በመገምገም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከሰራተኞች ጋር ውይይት አካሄደ። ጥቅምት 27 ቀን 2018ዓ.ም ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የ2018 በጀት አመት 1ኛ ሩብ አመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን በመገምገም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከሰራተኞች ጋር ውይይት አካሄደ። ውይይት መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ም/ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ፣ የፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሚሊዮን ኮራን፣ ም/ቢሮ ሀላፊ አቶ ክብረአለም ደምሴን ጨምሮ የፕሮሰስ ካውንስል አባላት እና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል። በመጀመሪያው ሩብ አመት ከዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች በተጨማሪ የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ እንዲሁም የከተማውን የስፖርት ልማት ስራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተሰሩ ስራዎች በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አቶ ዳዊት ገልፀዋል። በሩብ አመቱ ለወጣቶች በስራ እድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የማይድ ሴት ስልጠናዎች በመስጠት በከተማዋ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል 83 ፐርሰንቱ ወጣቶች መሆናቸውን አቶ ዳዊት ተናግረዋል። የከተማውን ወጣቶችና የስፖርት ቤተሰቦች በማስተባበር በክረምት በጎ ፈቃድ በአረንጓዴ አሻራ፣ በቤት እድሳት፣ በማዕድ ማጋራት እና በደም ልገሳን ጨምሮ በተሰራ ስራ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ሲሉ ም/ሀላፊው ገልፀዋል። የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላትን ጨምሮ በመዲናዋ የተካሄዱ ከተማ አቀፍና አለም አቀፍ ሁነቶች ካለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄዱ የከተማው ወጣቶቸና የስፖርት ቤተሰቦች አስተዋፅኦቸው ከፍተኛ እንደነበር አቶ ዳዊት ተናግረዋል። የቢሮውን የ2018 በጀት አመት የመጀመሪያ የሶስት ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት አቶ ጌታቸው አበባየሁ የእቅድና በጀት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር ዳይሬክተር አቅርበዋል። በወጣቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት፤ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማት፣ በታዳጊ ወጣቶች የስፖርት ስልጠና፣ በመህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና በስፖርታዊ ውድድሮች በሩብ አመቱ ስራዎች በሪፖርቱ ተመላክተዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ሰራተኞች በመጀመሪያ ሩብ አመት የተሰሩ ስራዎች አፈፃፀም ጥሩ መሆናቸውን ገልፀው በቀጣይ የቢሮውን ብሎም የከተማዋን ገፅታ የሚቀይሩና ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በተሳታፊዎች ለተነሱ ሀሳብና አስተያየቶች የቢሮው ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ የሰጠ ሲሆን በቀጣይ በወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲሁም የታዳጊ ወጣቶቾን የስፖርት ስልጠናን ጨምሮ በስፖርት መሰረተ ልማቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.