የወጣቶችን እና የሴቶችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጋራ ዓላማ ያነገቡ አደረጃጀቶች ቅንጅታዊ ርብርባቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ወ/ሮ አለምፀሀይ ሽፈራው
የወጣቶችን እና የሴቶችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጋራ ዓላማ ያነገቡ አደረጃጀቶች ቅንጅታዊ ርብርባቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ወ/ሮ አለምፀሀይ ሽፈራው ታህሳስ 17 ቀን 2018ዓ.ም ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ከከተማችን የወጣቶች እና የሴቶች አደረጃጀቶች ጋር በመሆን ታህሳስ 1 የጀመረውንና እስከ የካቲት 30 የሚቆየውን የ90 ቀናት የስራ ዕድል የንቅናቄ ስራዎች ዕቅድ እና አተገባበሩን የጋራ አድርገዋል። በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት ም/ ኃላፊና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አለምፀሀይ ሽፈራው በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት የንቅናቄ ዕቅዱ ስኬቶችን ለማጠናከር ፣ ከራዕያችን አኳያ ይበልጥ ለመትጋት ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ በቅርቡ ያስቀመጧቸውን ግቦች አልቆ ለመፈፀም እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል። . ይህ ዓመት እንደ አምስት ዓመት ሰፋፊ ተግባራት የሚፈፀሙበት፣ ተደራራቢ ተልዕኮዎች የሚከወኑበት መሆኑን ያወሱት ወ/ሮ አለምፀሀይ የዓመቱን ዕቅድ ከተያዘው ጊዜ ቀድሞ ለማሳካት የተጀመረውን ብርቱ ጥረት ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል። የወጣቶችን እና የሴቶችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጋራ ዓላማ ያነገቡ አደረጃጀቶች ቅንጅታዊ ርብርባቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገን ያስገነዘቡት ወ/ሮ አለምፀሀይ ዕቅዳችንን ማሳካት ምርጫ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ ሊገጥሙ የሚችሉ ማነቆዎችን የጋራ መፍትሄ እየሰጡ መጓዝ እንደሚገባ አመላክተዋል። ባለፉት ስድስት ወራት በከተማችን ከ169 ሺህ በላይ ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ የስራ ስምሪትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስፋው ለገሰ ባቀረቡት ሰነድ የተጠቀሰ ሲሆን ከተማችን ካሏት ፀጋዎች እንዲሁም ካለው የስራ አጥ ቁጥር አንፃር አሁንም ሰፊ ርብርብ እንደሚጠይቅ ተመላክቷል። በቅርቡ በክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ይፋ የተደረጉ ግቦችን ዕውን በማድረግ የህዝባችንን ተጠቃሚነት በማስፋት ልመናን እና ተረጅነትን ለማስወገድ በቴክኖሎጂ የታገዘ የስራ ዕድል ፈጠራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል። የስራ ዕድል ፈላጊዎችን በየብሎኩ እና ቤት ለቤት በመሄድ ጭምር ለማግኘት የሚደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ማስገኘቱን የጠቀሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች ለንቅናቄ ዕቅዱ ውጤታማ አተገባበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። በውይይቱ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት ም/ ኃላፊና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አለምፀሀይ ሽፈራው ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ፣ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ኃላፊ ወጣት መለሰ አባተ እና የወጣቶች እና የሴቶች ክንፍ እንዲሁም ፣ የሴቶች እና የወጣቶች ማህበር በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተገኝተዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.