ከ100 ሺህ በላይ ሴቶች የሚሳተፉበት የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እሁድ ይካሄዳል
ከ100 ሺህ በላይ ሴቶች የሚሳተፉበት የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እሁድ ይካሄዳል
የካቲት 26 ቀን 2018ዓ.ም ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ
"50ኛው ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነት እና ለበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ታላቅ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የፊታችን እሁድ የካቲት 29 ቀን እንደሚካሄድ ተገለጠ።
ይህ ታላቅ ስፖርታዊ መድረክ የሴቶችን ሁለንተናዊ እኩልነት ለማንፀባረቅና በሀገር ግንባታ ላይ ያላቸውን ሚና ለማጉላት ያለመ መሆኑ ታውቋል።
በጉጉት በሚጠበቀው በዚህ የሩጫ ውድድር ላይ ከ100 ሺህ በላይ ሴቶች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የውድድሩ መነሻ በአትላስ አካባቢ ሆኖ መድረሻውን ካሳንቺስ በሚገኘው የሴቶች አደባባይ እንደሚያደርግ ታውቋል።
ዝግጅቱ የሴቶችን ድምፅ ከፍ አድርጎ የሚያሰማ ከመሆኑም በላይ፣ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴንና ህብረትን የሚያጠናክር እንደሆነ ተገልጿል።
ውድድሩን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የጋራ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።
በዚህ መድረክ ላይ የከተማና የክፍለ ከተማ የዘርፉ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን፣ የዝግጅቱን መጠናቀቅና ለተሳታፊዎች የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን በተመለከተ ሰፊ ምክክር ተደርጓል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሁለቱ ቢሮ ኃላፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ የዘንድሮው የሴቶች ቀን በልዩ ሁኔታ እንዲከበርና የሴቶች የእኩልነት ጥያቄ በተግባር እንዲታይ የዚህ ስፖርታዊ መድረክ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ውድድሩ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.




አስተያየቶችዎን ይተዉት.