7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
መጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም | ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ
የፊታችን ግንቦት 2018 ዓ.ም የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ።
ቢሮው ይህንን ጥሪ ያስተላለፈው የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር "በወጣቶች ንቁ ተሳትፎ የደመቀ ምርጫ ለሀገራችን እምርታ" በሚል መሪ ቃል ዛሬ ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ነው። በመድረኩም ከ11ዱም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣትችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ወጣቶች ባለፉት ዓመታት በከተማዋ ለተመዘገቡ የልማትና የገጽታ ግንባታ ሥራዎች የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
ምርጫው ሀገረ መንግሥት የሚጸናበትና ዴሞክራሲያዊ ልምምድ የሚዳብርበት መድረክ በመሆኑ፣ ወጣቶች በሂደቱ ላይ በንቃት በመሳተፍ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አቶ አሰግደው አሳስበዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ክብርአለም ደምሴ በበኩላቸው፤ "ወጣቱ የምርጫ ካርድ በመውሰድ የዜግነት ግዴታውን ከመወጣት ባለፈ፣ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስኬታማነት በቁርጠኝነት መስራት አለበት" ብለዋል።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት በረከት ብርብርሳ በበኩላቸው፤ ማኅበሩ ከ500 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን፣ እስካሁንም ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑት የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል። ወጣቶች በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉም ሰፊ የግንዛቤ ማሳደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
ወጣቶች የምርጫ ካርድ በመውሰድና ድምፅ በመስጠት ብቻ ሳይወሰኑ፣ ሂደቱ ሰላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን የጠባቂነት ሚና ሊጫወቱ ይገባል። ማንኛውንም ግጭት ቀስቃሽ ድርጊቶችን በመከላከል፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው በሰከነና በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ግንባር ቀደም ኃላፊነት እንዳለባቸው በመድረኩ ተመላክቷል።
https://linktr.ee/YouthandSport1
Comments
ምንም አልተገኘም.





አስተያየቶችዎን ይተዉት.