ቢሮው ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ስትራቴጂካዊ የጋራ ሥራ ስምምነት ተፈራረመ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ስትራቴጂካዊ የጋራ ሥራ ስምምነት ተፈራረመ
ሰኔ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የከተማዋን የስፖርት ዕድገት ይበልጥ ለማሳደግ የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋትና የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችለውን ታሪካዊ የሁለትዮሽ መግባቢያ ሰነድ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ (AMN) ጋር ተፈራርሟል።
የሥራ ስምምነቱን የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃይለ ጊዮርጊስ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ በጋራ አረጋግጠውታል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቢሮ ኃላፊው አቶ አሰግደው ኃይለ ጊዮርጊስ ቢሮው የነደፋቸውን ታላላቅ ራዕዮችና ግቦች ለማሳካት ተተኪ ስፖርተኞችን በስፋት ለማፍራት እንዲሁም ወደ ሰፊው ማህበረሰብ በቀላሉ ለመድረስ የሚዲያ ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ይህ ስምምነት ለተቋሙ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
አቶ አሰግደው አክለውም አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በቅርቡ ባካሄደው መጠነ-ሰፊ የሪፎርም ሥራ ራሱን ይበልጥ እያጠናከረ መምጣቱን አንስተው፣ በተለይም የከተማዋን የስፖርት ቱሪዝም ዘርፍ በማላቅ ውድድሮችንና ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ሁነቶችን በቀጥታ ስርጭት በሁሉም የመገናኛ ብዙኃን አማራጮች ተደራሽ እያደረገ መሆኑን በአብነት ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ሚዲያው በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና ተወዳዳሪ በመሆኑ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ረገድ የሚኖረው ሚና የጎላ ነው ብለዋል።
የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ በበኩላቸው ተቋማቸው ከከተማዋ ፈጣን ልማትና ዕድገት ጋር አብሮ በማደግ ላይ ያለ ተወዳዳሪ ሚዲያ መሆኑን ገልጸው ወጣቶችና ስፖርት በቀጥታ ትውልድ ላይ የሚሰሩ ዘርፎች በመሆናቸውና ኤኤምኤንም "የትውልድ ድምፅ" በመሆኑ የሁለቱ ተቋማት ቅንጅት ትውልድን በማነጽ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.