የአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል

ከተማችን አዲስ አበባ በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱባት የፌዴራሉ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት የሚገኙባት ናት፡፡ በመሆኑም የወጣቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማሳደግና ስፖርትን ባህሉ ያደረገ፣ ጤናማ ዜጋ፣ ብቃት ያለው ስፖርተኛና ህብረተሰብን በመፍጠር የከተማዋን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እድገት ማፋጠን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡
መንግስትም የወጣቶችን እና የስፖርትን ጉዳይ እንደ ዋና የልማት አጀንዳ በመያዝ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ በአገሪቱ ብሎም በከተማችን በተደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር የተመዘገበው ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ እድገቱ ራሱ የፈጠራቸው አዳዲስ ፍላጎቶችና አስቀድመው በወጉ ያልተቀረፉ ችግሮች ተደማምረው አሁንም የወጣቶችን ዘርፈ ብዙና አንገብጋቢ ችግሮች በሚፈለገው ደረጃ መፍታት አልተቻለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ከከተማዋ ዕድገት አኳያ ሲታይ የስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከላት ማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከማስፋፋት፣ የስፖርት ማዘውተርያ ሥፍራዎችን ተደራሽ ከማድረግ፣ ከታችኛው ዕድሜ እርከን ጀምሮ ዘመናዊ ስልጠናን ከመስጠት፣ በገቢ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ከማድረግ እና ባለሀብቱ በስፖርት መሰረተ ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮች ባለመመቻቸታቸው በሚፈለገው መልኩ ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም፡፡
በዚህም በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዙሪያ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ውጤቶችና በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት አጋዥ የሚሆኑ መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋት፣ የታዩ የአደረጃጀትና የአሰራር ማነቆዎችን በመለየት፣ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንደገና ተደራጅቷል ፡፡